በ መቐለ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ዩኒቨርሲቲዎች አቅም ግንባታ ፕሮጀክት(capacity building of ethiopian agriculture project ) ፣ ካንሰስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (kansas state university) እና USAID ትብብር የተሰሩ ትላልቅ የምርምር ስራዎችን በ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ኣመራሮች እና የዘርፉ ባለሙያዎች ተጎበኙ ።
በምርምር ማእከሉ በተለያዩ የ ፓስታና ማካሮኒን የስንዴ ዝርያዎች ጨምሮ ከ ኣንድ ሺ(1000) በላይ የ ስንዴ እንዲሁም የተለያዩ የ ጤፍ ዝርያዎች ላይ በሰፊው ምርምር እየተደረገ ሲሆን በተለያዩ ለምርምሩ የተመረጡ ቦታዎች ላይ ለሞዴል ኣርሶኣደሮች በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ተብሏል።
ፕሮጀክቶቹ የምግብ ዋስትናን እና የአካባቢን ጥቅም በብዝሃ ህይወት እና በግብርና ዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ሲሆን ይህ ጅምር የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን መጠቀምን ያበረታታል፣ ባህላዊ እና ጥቅም ላይ ያልዋሉ ዝርያዎችን አጽንኦት በመስጠት የአካባቢን የግብርና ሥርዓት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይረዳል። በተጨማሪም የተለያዩ እና ከተለያዩ የአየር ሁኔታዎች ጋር የተጣጣሙ ዝርያዎችን በማካተት አርሶ አደሮች አካባቢን በመጠበቅ የበለጠ አስተማማኝ ምርት እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።
በ ጉብኝቱ የተገኙት ዶክተር ዓብደልቃድር ከድር የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ኣከዳሚክ ቫይስ ፕሬዝደንት እና ዶክተር እያሱ ያዘው የምርምር እና የማህበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕሬዝዳንት በጉብኝቱ እንደገለፁት እነዚህ የ ምርምር ስራዎች መቐለ ዩኒቨርሲቲ ቀድሞ ወደ ነበረበት ጥናትና ምርምር ዘርፍ ለመመለስ ትልቅ ኣስተዋፅኦ ከማድረግ ኣልፎ በ ኣካባቢው ለሚገኝ ኣርሶኣደር ማህበረሰብ ዝርያውን በማከፋፈል በምግብ እራሱን እንዲችልና የተሻለ ምርት የሚያስገኝለት ምርት ለይቶ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ያለው ጅማሮ ተጠንክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም በሰፊው ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን እና ለሚሰሩት ምርምሮችም ዩኒቨርሲቲው ኣጋዥ እንደሚሆንም ገልፀዋል።