ማሽነሪ ምራቾች

መቐለ ዩኒቨርሲቲ ከትግራይ ማሽነሪ አምራቾች ኢንደስትሪ ዘርፍ ማህበራት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራረመ።
መቐለ ዩኒቨርስቲ ከኢንዱስትሪው ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠናክር የመግባቢያ ሰነድ ከ70 በላይ የማሽነሪ አምራች ድርጅቶችን ካቀፈው የትግራይ ማሽነሪ አምራቾች ኢንደስትሪ ዘርፍ ማህበራት ጋር በዛሬው ዕለት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።


የዚህ ስምምነት ዋና አላማ የዩኒቨርሲቲ-ኢንዲስትሪ ትስስርን በማጠናክርና ወደ ተግባር በመለወጥ የትግራይ መልሶ ግንባታን ማረጋገጥና የክልሉን ብሎም የሃገሪቱን የማሽነሪ ማኑፋክቸሪንግ አቅም ማሳደግ ነው። ይህንን እውን ለማድረግ የተፈረመው ሰነድ በምርምር፣ እውቀትና ክህሎት የተመራ ጠንካራና ዘመናዊ የማሽነሪ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመፍጠር ግብ ያደረጉ የጋርዮሽ ስራዎችን ለመስራት ያለመ ሲሆን ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያክል አምራቾች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች የሚፈቱ ምርምሮችን መስራትና እና የማማከር አገልግሎት መስጠት፣ አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር፣ ለዘርፋ የሚመጥን በእውቀት፣ ክህሎትና ስነምግባር የታነፀ የተማረ የሰው ሃብት ማሰልጠን፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢንዳስትሪዎቹ የተግባር ልምምድና ስልጠና እንዲወስዱ ማድረግ እና የሰው እና ቁሳቁስ ሃብትን በማቀናጀት ለዘርፉ ሁለንታዊ እድገት ጥቅም ማዋል ናቸው። ይህ ስምምነት ከወረቀት ባለፈ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የስምምነቱ ተፈራራሚዎች፣ መንግስትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት አበክረው መስራት እንዳለባቸው በስነስርዓቱ ተገልጿል።